ሁላችንም እንደ ክርስትያንነታችን እና እንደ ኢትዮጵያዊነታች ለእመቤታችን ያለን ፍቅር ላቅ ያለ ነው፡፡ እንደውም ይህን የታዘቡ የውጭ ሀገር ሰዎች “ኢትዮጵያዊ ሰውነቱ ቢቆረጥ ከደሙ ጋር አብሮ ማርያም የሚል ስም ይገኛል፡፡” ብለዋል ይባላል፡፡ በእውነትም ከኛ ሕይወት ጋር መቆራኘቱ ግን ለሁሉም ሐቅ ነው፡፡ ነፍሰ ጡር ልጅ ልትወልድ ስታምጥ “ማርያም! ማርያም!”፣ ስትወልድ “እንኳን ማርያም ማረችሽ” “ማርያም ጭንሽን ታሙቀው” “ማርያም በሽልም ታውጣሽ” ትባላለች፡፡ በአራስነት ወራቷም “የማርያም አራስ” ተብላ ድንግል ማርያም በአደራ ትሰጣለች፡፡ አንድን ሰው አንዳች ነገር እንዲያደርግልን ሽተን ስንለምንም “እንደው ለእኔ እንደ ቆምህልኝ ማርያም ትቁምልህ” ብለን ስሟን ጠርተን እንማጸነዋለን፡፡ ሰማዩን ቀና ብለን ለኖኅ የተሰጠውን ውብ የቃል ኪዳን ምልክት ቀስተ ደመና ስናይም “የማርያም መቀነት” እንላለን፡፡
ሕፃናት ለብቻቸው ሲስቁ “ማርያም እያጫወተቻቸው ነው፡፡” ይባላል፡፡ ሕጻናቱም አድገው ሲጫወቱ ማምለጫ ፍለጋ “የማርያም መንገድ ስጡኝ!” ይባባላሉ፡፡ እኛም እንገዲህ በስሟ የምንታመንና፤ ጠርተናት የማታሳፍረንን የእመቤታችን የድንግል ማርያምን ስም ከፊት አድርገን ይህን ታላቅ ‘’የማርያም መንገድ’’ የተሰኘ የበጎ አድራጎት ፕሮጀክት ይዘን መጥተናል።
‘‘የማርያም መንገድ’’ የበጎ አድራጎት ፕሮጀክት የሚያተኩረው እመቤታችን የጭንቅ ቀን ደራሽ እንደ መሆኗ በዚህ አለም በጭንቅ፣ በመከራ፣ በመራብ፣ በመጎሳቆል እና በመታመም የህይወት ፈተናዎች ውስጥ ያሉ ሰዎችን ባለን ነገር እና እድል በሰጠችን መጠን ለስጋ እና ለነፍሳቸው አንድ የመውጫ እድል፣ አንድ የማምለጫ ቀዳዳ እንድንሰጣቸው (የማርያም መንገድ እንደንሰጣቸው) የተጀመረ ፕሮጀክት ነው።
በዚህም አመት እንደመነሻ ለ6 የተቸገሩ ቤተሰቦች የዚህ ፕሮጀክት ተጠቃሚ አድርጎ ደግፏል። በዚሀም በመጀመሪያው ዙር ድጋፍ ከተደረገላቸው ሰዎች አመርቂ የሆነ ውጤት መመልከት ችለናል።
“እንደልጅነት ጨዋታ ምሳሌ በመከራ እና በችግር ተይዘው የሚኖሩ ሰዎችን እድል ሰጥተን በማርያም መንገድ እናሳልፋቸው!”