free amp template

ቤተ ክርስቲያን የተጨነቁ እና የታመሙ ሰዎች መጠጊያ እንደመሆኗ የጤና ህክምና አገልግሎትን በላቀ ሁኔታ በነጻ ለተቸገሩ ሰዎች እና ለምዕመናን ተደራሽ ማድረግን ዋነኛ ዓላማ በማድረግ በሰ/ት/ቤታችን በጎ አድራጎት በተቋቋመው የጤና ባለሙያዎች ቡድን የተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎችን እናከናውናለን። ከነዚህም መካከል፦

  1. የደም ግፊት እና የስኳር መጠን መለካት፦ በየትኛውም እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ የማህበረሰቡን አካላት የደም ግፊት ቅድመ ምርመራ እና የስኳር መለካት አገልግሎትን በአጽዋማት፣ በበአላት እና በተመረጡ ቀናት በሰንበት ከቅዳሴ በኋላ በማድረግ ያሉበትን ሁኔታ ለይተን እንደ ደረጃው ሙያዊ ምክርን በመለገስ ፣ የተሻለ ምርመራ የሚያስፈልጋቸውን ወደ ጤና ተቋማት እንዲሄዱ በማድረግ፣ ክትትል የሚያስፈልጋቸውንም በመከታተል እየተሰራ ይገኛል።
  2. የተለያዩ የጤና እክሎች ላይ ከጤና ባለሙያዎች ጋር የማማከር አገልግሎት፦ በሰ/ት/ቤታችን ውስጥም ሆነ ውጭ በተለያዩ ፊልዶች ላይ ያሉ ጤና ባለሙያዎችን በማካተት ትኩረት የሚሹ የጤና እክሎችን በመለየት የማማከር አገልግሎት እየሰጠን እንገኛለን።
  3. የጤና መረጃዎችን የያዙ በራሪ ወረቀቶችን ተደራሽ ማድረግ፦ በማህበረሰቡ ላይ በብዛት የሚስተዋሉ ህመሞች ውስጥ ዋነኛ የሆኑትን እንደ ሳንባ ነቀርሳ፣ ስኳር ህመም፣ ደም ግፊት እና ስትሮክ ላይ ግንዛቤን ለማስጨበጥ አመቺ እንዲሁም ለመረዳት ቀላል በሆነ መንገድ ተመርጠው የተዘጋጁ በራሪ ወረቀቶች ተዘጋጅተው ለምዕመናን ቀርበዋል።
  4. ተጨማሪ አገልግሎቶችን በማበርከት፦  ተጨማሪ የላብራቶሪ ምርመራ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ወጪያቸውን የበጎ አድራጎት ጽ/ቤቱ በመሸፈን አገልግሎቱን እንዲያገኙ ያደርጋል። በስነ አእምሮ የተሻለ ህክምናን ለሚሹ፣ የጭንቀት እና የመረበሽ ህመም በመለየት በአቅራቢያች ከሚገኝ የጤና ተቋም እና ባለሙያ ጋር በማገናኘት የተሻለ ህክምና እንዲያገኙ ያደርጋል። በሃኪም ትእዛዝ መድሃኒት እንዲወስዱ የታዘዘላቸው ነገር ግን ለመግዛት አቅማቸው ለማይፈቅድ ሰዎች በጎ አድራጎት ጽ/ቤቱ የመድሃኒት ወጪን ሲሸፍን ቆይቷል። በበጎ አድራጎት ጽ/ቤቱ በኩል ህክምና እንዲያገኙ የተደረጉ ሰዎች ለክትትሉ የሚያስፈልግ የትራንስፖርት ወጪ እርዳታ ይደረግላቸዋል።  

© Copyright 2024 Finot Charity - All Rights Reserved